የአብክመ ቤቶች ልማት ደርጅት እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የግንባታ ማማከር ውል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት በባህርዳር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሚያስገነባው ዘመናዊ የሕንጻ ግንባታ የማማከር ውል ስምምነት ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በባህርዳር ከተማ ተፈራርመዋል፡፡

የግንባታ አማካሪነት የውል ስምምነቱን የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አበረ ሙጨ እና የፈዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት የአልሙኒየም ፎርም ወርክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሚያስገነባው የግንባታ ፕሮጀክት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሙሉ የማመከር ሥራ የሚያከናውን ይሆናል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን ሪፎርም መነሻ በማድረግ በተቋም ግንባታ፣ በግንባታው ኢንዱስትሪ በቤት ልማት እና በማመከር ረገድ ግንባር ቀደም የሆነ ተቋም ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩትን የጥራት፣ የጊዜና እና የዋጋ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት ከኦቪድ ካምፓኒ ጋር ኮርፖሬሽኑ በጥምረት፣ የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ18 ወራት ግዙፍ የመኖሪያ መንደር መገንባት መቻሉን ገልጸዋል። በአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት በሚገነባው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክትም ጥራትን፣ ጊዜን እና ዋጋን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ኮርፖሬሽኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

አገራችን የተለመችው የብልጽግና ጉዞ የሚሳካው ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ኮርፖሬሽኑ ደረጃ አንድ ኮንትራክተር እና አማካሪ በመሆኑ ከግንባታ ቅድመ-ዝግጅት እስከፍጻሜ አስፈላጊውን የማመከር አገልግሎት እንደሚሰጥ ዋና አረጋግጠዋል፡፡

የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አበረ ሙጨ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በአማካሪነት የተመረጠው በርካታ መስፈርቶችን ያሟላ፣ ውጤታማ የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ልምድ ያካበተ ተቋም በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ በ18 ወራት ግዙፍ የመኖሪያ መንደር በመገንባት የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ውጤታማ የሆነ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተቋም በመሆኑ ከኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚተገበረው የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ የቤት ግንባታ የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት ከፕሮጀክት ማማከር በዘለለ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የአብክመ ቤቶች ልማት ድርጅት

ነሀሴ/2014 ዓ.ም

   ባ/ዳር

betochi